ግንቦት ሰባት ና

ዛሬ ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቼ ነበር፡፡ የተቃውሞ ሰልፍ ስል መንግስትን ለመቃወም ሳይሆን በአረብ አገር በኢትዮጵያውያን ላይ እየተደረገ ባለው ሰብዓዊነት በጎደለው ድርጊት ላይ ከህዝብ ጋር ለማልቀስ፡፡ አዎን ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ ተገኝቼ የበኩሌን የኢትዮጵያዊነትን ዱላ ለመቅመስ በሳውዲ ኢምባሲ አካባቢ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጀምሬ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ ሰዓቱ እንደደረሰም መሰባሰብ ጀመርንና ድምፅ ማሰማት ጀመርን፡፡ አንድ ሁለት ዘበኛ የሚመስሉ የፌዴራል ፖሊሶች ከአካባቢያቸው ፎቅ ብለን ወደ ኢምባሲው መጠጋት እንደምንችል ሲነግሩን እኔም ፖሊሶቹ ኢትዮጵያዊነት የተሰማቸው መስሎኝ የፊቱን መስመር ያዝኩ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችም ጥቁር የሃዘን ልብስ ለብሰው ገና የያዙትን መፈክር ማውጣት ሲጀምሩ “ልቀቁ፤ ራቁ” የሚሉ ሌሎች የፌዴራል ፖሊሶች አዋከቡን፡፡ ብዛት ያለው መኪና በኣካባቢው የሚመላለስበት መንገድ በመሆኑ መኪና ውስጥ ያሉትን ሰዎች ገፅታ ማየት ችዬአለሁ፡፡ ሁሉም አዝኗል፡፡ ሌላም ነገር አንብቤባቸዋለሁ፡፡ ሁሉም ተስፋ የቆረጠ ፊት ነው የሚያሳዩት፡፡ ምንአልባት እንደማይሆን ቀድመው አውቀው ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ጥሪው ሳይደርሳቸው ቀርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ማንም ፊት ላይ የደስታ/ግርምት ስሜት አይታይም፡፡ ለኔ ግን በተቃውሞ ሰልፍ ላይ መውጣት ለመጀመሪያዬ ስለሆነ የምሰማው ነገር በኔ እንዲደርስ ተመኝቼ ስለነበር የፊት መስመሩን እንደያዝኩ ድብድቡ ተጀመረ፡፡

“መንግስት የለም ወይ፣ መንግስት የለም ወይ?!” ይህን ቃል በሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሰማሁት ሃረግ ስለሆነ በወቅቱ ስሜቴን አልነካውም ነበር፡፡ “መንግስት የለም ወይ?!” ማለት ምን ማለት ነው፡፡ የሞራል ጥያቄ ነው እኮ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “የኔ ስጋ መብላት ወንድሞቼን የሚያሳስት ከሆነ እድሜ ልኬን ስጋ አልበላም” እንዳለው ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የሃዋሪያዊት ቤተ ክርስቲያን አማኝ ስለነበረ ቃሉንም ስለሚያውቅ ምእመናን እርሱን እያዩ እንዳይሳሳቱ ቦታውን ቢለቅ፣ የሚያምኑት እምነት ያላቸውም ሆነ የሌላቸው የመንግስት አካላትም ቢሆኑ በተማሩት ትምህርት መሰረት በያዙት ወንበር በብቃት መስራት ካልቻሉ፣ ባጠቃላይ መንግስት መሆን ካልቻሉ ልቀቁ ማለት ይመስለኛል፡፡ ይህን ልል ያስቻለኝ መንግስት ማለት ህዝብ ማለት ነው ብለው ስላስተማሩን ያውቁታል ብዬ ነው፡፡

ወደ ተነሳሁበት ስመለስ፤ ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባሎች መሃል “አቦ ይሄ ሰውዬ ነው የመጣው” ሲሉ ገረመኝ፡፡ አንድ ጨካኝ ሲቪል የለበሰ ሰው “ምን ትጠብቃላችሁ?” ሲላቸው ቃታው እንደተሳበ አውቶማቲክ ማሽን መሳሪያ የፌዴራል ፖሊሶች ዱላ ጀመሩ፡፡ ጭንቅላት፣ ፊት፣ እጅ፣ ባጠቃላይ ከወገብ በላይ የሆነ አካልን መደብደብ ጀመሩ፡፡ ፈዝዤ መመልከት ጀመርኩ፡፡ እኔን ቆርጠው(ትተውኝ) ሌሎቹን መደብደብ ተያያዙት፡፡ በቪዲዮ ሳይ የነበረውን ክስተት ወገን በወገኑ ላይ ሲፈፅም በአይኔ በብረቱ ተመለከትኩ፡፡ እናም አልኩ እንደዚህ እየተደበደቡና እየተገደሉ የታገሉ ሰዎች ግዜ ቢያድላቸውና ስልጣን ቢይዙ፤ ቢጨማለቁ፣ ስልጣንን ያለአግባብ ቢጠቀሙ ልንወቅሳቸው አይገባንም፡፡ ልብ በሉ፡፡ በአካባቢው ያሉት ሰዎች ቢረባረቡና ፖሊሶቹን ቢመክቷቸው ስልጣን የጋራ ሊሆን ይገባዋል ብዬ ልከራከር እችላለሁ፡፡

አጠገቤ አንዲት ሴት ኡኡ ትላለች፣ ያልተደበደበ ወጣት ወይ ሽማግሌ የለም፡፡ እኔ ደግሞ የደህንነት አባል ልምሰላችው አላውቅም እንጃ ማህላቸው አስገብተውኝ ሌሎቹን ግን መሬት ለመሬት እየጎተቱ፣ እየደበደቡ፣ “ተነስ!” እያሉ አናት አናቱን ይመቱታል፡፡ ከተፈጥሮዬ ሰው ሲመታ ማየት አልችልም፡፡ ማህል የመገግባት ፀባይ አለኝ፡፡ ዛሬ ግን አልቻልኩም፡፡ ልሞክረው አስቤ ነበር፡፡ ፈራሁ፡፡ ብቻዬን ነኝ፡፡ እነሱ በግሩፕ ነው የሚደበድቡት፡፡ እውነትም መንግስት የለም፡፡ መንግስት ማለት ህዝብ፤ ህዝብም ማለት መንግስት ከሆነ ህዝብም የለም፡፡ አዎ ያቺ ኡኡ የምትለው ሴት እንዳለችው ለኳስ እንጂ ለወገን ስቃይና ሞት ባንዲራ የሚያወጣ፣ በህግ አምላክ የሚል፣ በባንዲራው የሚል የለም፡፡ ባንዲራም የለም፡፡ ፖሊስም የለም፡፡ የህዝብን ደህንነት የሚጠብቅ አካልም የለም፡፡

ግን አንድ ነገር አለ፡፡ ለዩትዩብ የሚሆን ቪዲዮ የሚቀርፅ፡፡ 

Advertisements

Leave a Reply

Fill in your details below or click an icon to log in:

WordPress.com Logo

You are commenting using your WordPress.com account. Log Out /  Change )

Google+ photo

You are commenting using your Google+ account. Log Out /  Change )

Twitter picture

You are commenting using your Twitter account. Log Out /  Change )

Facebook photo

You are commenting using your Facebook account. Log Out /  Change )

w

Connecting to %s