ግንቦት ሰባት ና

ዛሬ ለተቃውሞ ሰላማዊ ሰልፍ ወጥቼ ነበር፡፡ የተቃውሞ ሰልፍ ስል መንግስትን ለመቃወም ሳይሆን በአረብ አገር በኢትዮጵያውያን ላይ እየተደረገ ባለው ሰብዓዊነት በጎደለው ድርጊት ላይ ከህዝብ ጋር ለማልቀስ፡፡ አዎን ሰማያዊ ፓርቲ በጠራው ሰልፍ ላይ ተገኝቼ የበኩሌን የኢትዮጵያዊነትን ዱላ ለመቅመስ በሳውዲ ኢምባሲ አካባቢ ከጠዋቱ ሶስት ሰዓት ላይ ጀምሬ መጠባበቅ ጀመርኩ፡፡ ሰዓቱ እንደደረሰም መሰባሰብ ጀመርንና ድምፅ ማሰማት ጀመርን፡፡ አንድ ሁለት ዘበኛ የሚመስሉ የፌዴራል ፖሊሶች ከአካባቢያቸው ፎቅ ብለን ወደ ኢምባሲው መጠጋት እንደምንችል ሲነግሩን እኔም ፖሊሶቹ ኢትዮጵያዊነት የተሰማቸው መስሎኝ የፊቱን መስመር ያዝኩ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችም ጥቁር የሃዘን ልብስ ለብሰው ገና የያዙትን መፈክር ማውጣት ሲጀምሩ “ልቀቁ፤ ራቁ” የሚሉ ሌሎች የፌዴራል ፖሊሶች አዋከቡን፡፡ ብዛት ያለው መኪና በኣካባቢው የሚመላለስበት መንገድ በመሆኑ መኪና ውስጥ ያሉትን ሰዎች ገፅታ ማየት ችዬአለሁ፡፡ ሁሉም አዝኗል፡፡ ሌላም ነገር አንብቤባቸዋለሁ፡፡ ሁሉም ተስፋ የቆረጠ ፊት ነው የሚያሳዩት፡፡ ምንአልባት እንደማይሆን ቀድመው አውቀው ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ጥሪው ሳይደርሳቸው ቀርቶ ሊሆን ይችላል፡፡ ቢሆንም ግን ማንም ፊት ላይ የደስታ/ግርምት ስሜት አይታይም፡፡ ለኔ ግን በተቃውሞ ሰልፍ ላይ መውጣት ለመጀመሪያዬ ስለሆነ የምሰማው ነገር በኔ እንዲደርስ ተመኝቼ ስለነበር የፊት መስመሩን እንደያዝኩ ድብድቡ ተጀመረ፡፡

“መንግስት የለም ወይ፣ መንግስት የለም ወይ?!” ይህን ቃል በሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የሰማሁት ሃረግ ስለሆነ በወቅቱ ስሜቴን አልነካውም ነበር፡፡ “መንግስት የለም ወይ?!” ማለት ምን ማለት ነው፡፡ የሞራል ጥያቄ ነው እኮ፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “የኔ ስጋ መብላት ወንድሞቼን የሚያሳስት ከሆነ እድሜ ልኬን ስጋ አልበላም” እንዳለው ሁሉ ጠቅላይ ሚኒስቴር ኃ/ማሪያም ደሳለኝ የሃዋሪያዊት ቤተ ክርስቲያን አማኝ ስለነበረ ቃሉንም ስለሚያውቅ ምእመናን እርሱን እያዩ እንዳይሳሳቱ ቦታውን ቢለቅ፣ የሚያምኑት እምነት ያላቸውም ሆነ የሌላቸው የመንግስት አካላትም ቢሆኑ በተማሩት ትምህርት መሰረት በያዙት ወንበር በብቃት መስራት ካልቻሉ፣ ባጠቃላይ መንግስት መሆን ካልቻሉ ልቀቁ ማለት ይመስለኛል፡፡ ይህን ልል ያስቻለኝ መንግስት ማለት ህዝብ ማለት ነው ብለው ስላስተማሩን ያውቁታል ብዬ ነው፡፡

ወደ ተነሳሁበት ስመለስ፤ ከሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችና አባሎች መሃል “አቦ ይሄ ሰውዬ ነው የመጣው” ሲሉ ገረመኝ፡፡ አንድ ጨካኝ ሲቪል የለበሰ ሰው “ምን ትጠብቃላችሁ?” ሲላቸው ቃታው እንደተሳበ አውቶማቲክ ማሽን መሳሪያ የፌዴራል ፖሊሶች ዱላ ጀመሩ፡፡ ጭንቅላት፣ ፊት፣ እጅ፣ ባጠቃላይ ከወገብ በላይ የሆነ አካልን መደብደብ ጀመሩ፡፡ ፈዝዤ መመልከት ጀመርኩ፡፡ እኔን ቆርጠው(ትተውኝ) ሌሎቹን መደብደብ ተያያዙት፡፡ በቪዲዮ ሳይ የነበረውን ክስተት ወገን በወገኑ ላይ ሲፈፅም በአይኔ በብረቱ ተመለከትኩ፡፡ እናም አልኩ እንደዚህ እየተደበደቡና እየተገደሉ የታገሉ ሰዎች ግዜ ቢያድላቸውና ስልጣን ቢይዙ፤ ቢጨማለቁ፣ ስልጣንን ያለአግባብ ቢጠቀሙ ልንወቅሳቸው አይገባንም፡፡ ልብ በሉ፡፡ በአካባቢው ያሉት ሰዎች ቢረባረቡና ፖሊሶቹን ቢመክቷቸው ስልጣን የጋራ ሊሆን ይገባዋል ብዬ ልከራከር እችላለሁ፡፡

አጠገቤ አንዲት ሴት ኡኡ ትላለች፣ ያልተደበደበ ወጣት ወይ ሽማግሌ የለም፡፡ እኔ ደግሞ የደህንነት አባል ልምሰላችው አላውቅም እንጃ ማህላቸው አስገብተውኝ ሌሎቹን ግን መሬት ለመሬት እየጎተቱ፣ እየደበደቡ፣ “ተነስ!” እያሉ አናት አናቱን ይመቱታል፡፡ ከተፈጥሮዬ ሰው ሲመታ ማየት አልችልም፡፡ ማህል የመገግባት ፀባይ አለኝ፡፡ ዛሬ ግን አልቻልኩም፡፡ ልሞክረው አስቤ ነበር፡፡ ፈራሁ፡፡ ብቻዬን ነኝ፡፡ እነሱ በግሩፕ ነው የሚደበድቡት፡፡ እውነትም መንግስት የለም፡፡ መንግስት ማለት ህዝብ፤ ህዝብም ማለት መንግስት ከሆነ ህዝብም የለም፡፡ አዎ ያቺ ኡኡ የምትለው ሴት እንዳለችው ለኳስ እንጂ ለወገን ስቃይና ሞት ባንዲራ የሚያወጣ፣ በህግ አምላክ የሚል፣ በባንዲራው የሚል የለም፡፡ ባንዲራም የለም፡፡ ፖሊስም የለም፡፡ የህዝብን ደህንነት የሚጠብቅ አካልም የለም፡፡

ግን አንድ ነገር አለ፡፡ ለዩትዩብ የሚሆን ቪዲዮ የሚቀርፅ፡፡ 

Advertisements

ፖለቲካ ለካ ወረርሽኝ ነው?

አቤ ቶኪቻው በተናገረው ያንን ሁሉ ድንፋታ ሳይ ምን ቢሆን እነኝህ ሰዎች ደስ ይላቸዋል? እስኪ ቢሳካላቸው ምን ይከተላል? ብዬ ማሰብ ጀመርኩ

እስኪ ኦሮሚያን ተገንጥላ እንያት

 1. በዚህ ወቅት ያለው የኦሮሚያ ክፍል ይቀጥላል
 2. በኦሮሚያ ክልል ያሉ ማንኛውም የሌላ ብሄር ተወላጆች ክልሉን ለቀው እንዲሄዱ ይገደዳሉ
 3. ሰሜን ሸዋ ያሉት (ኦሮሚያ ልዩ ዞን) ኦሮሞዎች በኦሮሚያ ክልል እንዲጠቃለሉ ይሞከራል
 4. ባቲ፣ ወረባቦ፣ ወረ ኢሉ፣ ጃማ፣አለማጣ እናም የመሳሰሉት ወረዳዎች ውስጥ ያሉትን ኦሮሞዎች ለማጠቃለል ይሞከራል
 5. በደቡብ ክልል ያሉትንም የኦሮሞ ተወላጆች፣ በጌዴኦና ወላይታ የተከበቡትን ጉጂዎችንና ሌሎችንም ለማጠቃለል ወይንም ወደ ኦሮሚያ ሌሎች ከተሞች ለማምጣት ይሞከራል
 6. በሶማሌ ክልል ውስጥ ያሉትንም ለማውጣት ወይንም ለመርሳት ይሞከራል
 7. ሌሎችም ሌሎችም

ስለዚህ ምን ሊሆን ይችላል?

 1. የኦሮሞ ነፃ አውጪ በጣም ሃይለኛ (powerful) ይሆናል
 2. ከላይ የጠቀስኳቸውን ወረዳዎችና ዞኖችን ለማካተት በሚደረገው ሙከራ የህዝብ ለህዝብ ጦርነት ይመጣል (civil war)፡፡ ለምሳሌ ከሸኖ እስከ ከሚሴ ኦሮሞ ያልሆኑ ብዙ ህዝቦች አሉ፡፡ ይህ በደቡብና በሶማሊያ ክልልም እንዲሁ የህዝብ ለህዝብ ችግር ይፈጠራል
 3. ስልጣንና ሃይል እስካለው ድረስ ኢትዮጵያን ባጠቃላይ የኦሮሞ ነፃ አውጪ ግንባር ይገዛል
 4. ሌላ የጎሳ ፓርቲ ኢትዮጵያን ለሚከተሉት ሌላ የስቃይ አመታት ይገዛል
 5. የኦሮሞም ሆነ ሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄ ግን አይመለስም

የህዝብ ጥያቄ ምንድን ነው?

 • አቶ ኦባንግ ሚቶ መልሰውታል
 1.  የፍቅር ጥያቄ ነው
  1.     በፍቅር እንኑር
  2.  ሰው በሰውነቱ የትም ሰርቶ ይኑር፡፡ ልክ ዲያስፖራዎቻችን በሰላም በሰው አገር ሰርታችሁ ተርፎአችሁ ለቤተሰቦቻችሁ እንደምትልኩት ማለት ነው፡፡
 2.  የፖለቲካ ጥያቄ የለውም
  1.    ማንም ይግዛው ማንም በፍቅር፣ በሰላም፣ ሳይገድለው፣ ሳያሳድደው፣ በሃይማኖቱ ሳያገለው፣ በባህሉ ሳይንቀው ይሁን እንጂ

 

 • ታማኝ በየነ መልሶታል
 1. “ህዝብ ተበድሏል? አዎ ተበድሏል፡፡ ስለዚህ ምን እናድርግ? ተከባብረን አንዳችን ካንዳችን እየተከባበርን አብረን እንኑራ!!”

መልእክት አለኝ

 1. ህወሃት ትግራይን ነጻ አወጣለሁ ብሎ ኢትዮጵያን የገዛው ትግራይ ካለኢትዮጵያዊነት ምንም እንዳልሆነች ተፈጥሮ አስገድዶት ነው
 2. ኦነግም ከህወሃት ተሞክሮ ወስዶ ህዝብ ከህዝብ ከማጨራረስ፤ ከዚህ በፊት በኛ ላይ ደረሰ የሚለውን ሰቆቃና ችግር በሌላው ላይ ከማድረስ ቢቆጠብ ደስ ይለኛል

Investment in Ethiopia

ያ…..ኛው ገበሬ

ያላግባብ የሚያርሰው ትምህርት የሌለው ሰው

ድንግሊቷን መሬት ያልተንከባከበው

በድቅድቅ ጨለማ ሩቅ የሚኖረው

ለውጥ ያልገባው ሰው

ስልጣኔ የሌለው

ገላውን እራፊ ጨርቅ ነክቶት የማያውቀው

ተቆርቋሪም ሆነ ጠባቂ የሌለው

ቦታውንም ይልቀቅ!

በረሃ ይከተት!

ልጆቹም ይለቁ!

ዘሩም ይሁን ተረት፡፡

በረሃ አቅንቶ ሊኖር ተደላድሎ

ኢትዮጵያን ሃገሬ ለምለሚቷ ብሎ

ቁጥቋጦ መንጥሮ አለትን ፈንቅሎ

የማይረባውን ጎጆ አጥፍቶ አቃጥሎ፤

ኢኮኖሚያችንን የሚያመነጥቀው

የስልጣኔን ጎዳና ሊያሳየን የመጣው

የህንዱ ገበሬ አገር የሚያለማው

ይውሰደው መሬቱን ሳያየው ሳያውቀው

የምዕተ ዓመቱ ድርድር እኮ ነው፡፡

ይረሰው ይረሰው ደጋግሞ ይረሰው

እስከሚገኝለት ወግድ የሚለው ሰው፡፡

ይረሰው ማሳውን ጨምሮ ጓሮውን

እርሱ ምን ቸገረው አይደለ ብቻውን፡፡

ይጠቀም ጉልበትን ከተፈናቀለው

ቀዬውን በብላሽ በገፍ ከወሰደው

ግን እላለሁኝ

ሰው በሰው ይነሳል

ይህም ቤት ይፈርሳል!!